ጋዜጣዊ መግለጫ
Press Release
በኦሮሚያ ክልል በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ፕሮግራማዊ ተልእኮ እየተመራ ያለው የአማራን ዘር የማጥፋት ኢ-ሰብዓዊና አፀያፊ ድርጊት ሊቆም ይገባል
ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ከጭጨፋ የተረፉ የ19 ቀበሌ ነዋሪዎች 40 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘው ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ መጠለላቸው ታውቋል፡፡ ከሞት አምልጠው ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁንም ለሕይዎታችን አስተማማኝ ነገር የለም በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ዓመታትን ያስቆጠረው የአማራ ተወላጆች ጭፍጨፋ አሁንም ድረስ መፍትሔ ያላገኘው፣ ጥቃቱ በኦህዴድ/ብልፅግና መንግስት የሚመራ በመሆኑ እንደሆነ ገሃድ እየወጣ መጥቷል፡፡
በሆሮጉድሩ ወለጋ በጃርቴ ጃርዴጋ ወረዳ በሻምቡ ከተማ እና ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ በዚህ ሳምንት ከፍተኛ ጥቃት ከተደረገባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ ምስራቅ ወለጋ ዞን የጊዳ ኪረሙ ወረዳ መቀመጫ በሆነችው ኪረሙ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳያውሉ እንቅፋት ፈጥራችኋል በሚል ሰበብ ታስረው የነበሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች በጅምላ መረሸናቸውን ከጅምላ ጭፍጨፋው አምልጠው የወጡ የአይን እማኞች መናገራችው በሚዲያ ተዘግቧል ።
ከህዳር 09/2015 ዓ/ም ጀምሮ በከተማዋ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታስረው የነበሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ እስረኞች ህዳር 20 ለህዳር 21 አጥቢያ በጅምላ መረሸናቸው አይዘነጋም። በህዳር ወር ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ሽብርተኛው ሸኔ እና የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ተቀናጅተው ባካሄዱት ኢ- ሰብአዊ ዘመቻ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሕይወታቸው ተቀጥፏል፤ከፍተኛ መፈናቀልም ደርሶባቸዋል፡፡
አማራን የመጨፍጨፍ እና የማፈናቃሉን አፀያፊና ዘረኛ ድርጊት የሚያስተባብሉ እና ሥራዬ ብለው የሀስት ዘመቻ የሚያናፍሱ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች፣ በተለይም የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግሬስ ሁለቱ ምክትል ሊቃነመናብርት እና የኦነግ የተለያዩ ክንፎች መሪዎች እና እነሱ የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጀው ከሕወሓት ቡድን ጋር በደቡብ አፍሪካ መደራደሩን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የአማራዎች ጭፍጨፋ ተጠናክሮ መቀጠሉ የአደባባይ ክንውን ሆኗል፡፡ የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሚዪኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በቅርቡ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ መንግስት ከኦነግ ሸኔ ታጣቂ ሽብርተኞች ጋር እንደማይደራደር እና ከአባ ገዳዎች ምሕረት ጠይቀው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን መግለፁ አይዘነጋም፡፡ ይህ አባባል የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በስውር ባሰማራው በሸኔ ላይ የሚጨክን ልብ የሌለው መሆኑን በግልፅ ያመለክታል፡፡ በተለይም በምስራቅ ወለጋ እና በአካባቢው ግድያ እና ዘረፋው አሁንም እየቀጠለ መሆኑን የሚገልፁት የጥቃቱ ሰለባዎች፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሕይታቸውን ለማትረፍ ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ ተጠልለው የሚገኙ ንፁሐንን መንግሥት የመከላከያ ሰራዊትን ወደ ቦታው ድረስ ልኮ ከሞት እንዲታደጋቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አዳማጭ መንግሥት ያላገኙ ስለመሆኑ በገሃድ እየታዬ ነው፡፡
የተለያዩ ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች መንግሥት ለምን ከሼኔ ጋር አይደራደርም በሚል ድርድር እንዲካሄድ እየገፋፋ ይገኛሉ፡፡ አማራ ኦሮሞን በቅኝ ግዛት ገዝቶታል በሚል የሃሰት ትርክት አስተሳሰባቸውን ያዛቡባቸውን የኦሮሞ ወጣቶች “ፋኖ ወደ ኦሮሞ ክልል ገብቶ ግድያ እየፈፀመ ነው” በሚል የሃሰት ዘመቻ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ተማሪዎች አመፅ እንዲቀሰቀሱ በመገፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ዘመቻቸው የአመለካከት አምሳያቸው የሆነው ህውሓት በፋኖ ላይ የከፈተውን የሃሰት ውንጀላ በማጠናከር የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት መከላከያ ሠራዊትን በፋኖ ላይ እንዲያዘምት በመቀስቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
እንደሚታወቀው በወለጋ እና በሰሜን ሸዋ አካባቢ እራሳቸውን ከህልውና ጥፋት እየተከላከሉ ያሉት በግፍ መገደልና መጠቃት ያንገሸገሻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንጅ ከአማራ ክልል የተነሱ ፋኖዎች እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ የፋኖን ስም ማጠልሸት የኦነግ – ብልጽግና፣ የኦነግ፣ የህወሓት እና የኦፌኮ የቀን ተቀን ተግባር መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ይህም እነዚህ ድርጅቶች ከአማራ የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እና በኢትዮጵያ ክስመት የትግራይ እና የኦሮምያ ሪፖብሊኮችን ለማዋለድ ሲመሠረቱ ጀምሮ ይዘው የተነሱትን የፖለቲካ ዓላማ እስካሁን ድረስ እያራመዱት እንደሚገኙ የሚያሳይ ተጨባጭ ክንውን ነው፡፡ ይህ አካሄዳቸው ህወሓት፣ ኦህዴድና ኦነግ የፖለቲካ ዓላማ አንድነት ያላቸው ፀረ- ኢትዮጵያ ድርጅቶች መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡
ፓርቲያችን ባልደራስ በወለጋም ሆነ በሌሎች የኦሮምያ አካባቢዎች ማቆምያ በሌለው ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን የአማራን ዘር የማጥፋት መንግሥታዊ መር ዘመቻ በፅኑ እየተቃወመ፣ የአማራው ማህበረሰብ ህልውናውን ከጥፋት ለመከላከል እያደረገ ያለው ተድጋሎ ተገቢ እና ህጋዊ መሆኑን በመግለፅ፣ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ባልደራስ የዩኒቨርስቲ መምህራን የጀመሩት የሥራ ማቆም አድማ ለመብታቸው መከበር እያደረጉ ያሉት ተቃውሞ ህጋዊ እና ሰላማዊ በመሆኑ፣ ከጎናቸው የሚቆም መሆኑን ለመግለፅ ይፈልጋል፡፡
የደራ አማራን የዘር ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
የሰላም ድርድሩን አስመልክቶ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ።
1. በድርድሩ የአማራና አፋር ማህበረሰቦችን ጥቅም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሂደቱ ተሳታፊ መሆን ሲገባቸዉ፣ይህ እንዲሆን አልተደረገም። ፓርቲያችን ባልደራስ ከህዝብ ጀርባ የተደረገ፣ ተጎጅ ማህበረሰቦችን ያላካተተ የጓዳ ድርድር እና ስምምነት ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ያስገኛል የሚል እምነት የለዉም።
2. በደቡብ አፍሪካዉ ድርድር በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ያለዉ ልዩነት ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ሁኗል። ይህ የስምምነቱ አንቀጽ ህወሃት ከህገመንግስቱ በፊት ከአማራዉ ታሪካዊ ይዞታዎች በሃይል ነጥቆ የያዛቸዉን ወልቃይት እና ራያን ወደ ትግራይ ክልል ማስመለሰን ግብ አድርጎ የተቀረጸ ነዉ። ይህ አንቀጽ ሌላ ዙር ግጭትና ጦርነት የሚቀሰቀስና ሃገራችን የሚያስፈልጋትን ሰላም እንዳታገኝ የሚያረጋት በመሆኑ፣ ባልደራስ ይህን የስምምነቱን አንቀጽ አጥብቆ ይቃወማል።
3. በአማራ ክልል በገለልተኛ አካላት የተጠና ጥናት በፌደራል መንግስት እና በአማራ ክልላዊ አስተዳደር ተደጋጋሚ የክተት ጥሪ መነሻነት የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ሉአላዊነት አለመገሰስ፣ለህልውናዉ መጠበቅ እና ለሰብአዊ ክብሩ መከበር ሲል ባካሄደዉ ተጋድሎ ወደ 1 ትሪሊዬን የሚገመት የሀብት ውድመት እንደደረሰበት አመላክቷል። በስምምነቱ ዉስጥ ለዚህ ጉዳት ፍትሃዊ ተጠያቂነት ሊኖር እና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ሊካተት ሲገባ አልተካተተም። ይህን ስምምነት በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስገደዱት የምዕራቡ አለም እና በተለየም የአሜሪካ መንግስት በጦርነቱ ምክንያት ትግራይን ጨምሮ በአማራና እና በአፋር ክልሎች ለደረሰዉ እጅግ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን እርዳታ እንዲሰጡ በስምምነቱ ዉስጥ ማሻሻያ እንዲካተት ሊደረግ እንደሚገባ ፓርቲያችን ባልደራስ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
ለባልደራስ አባላት እና ደጋፊዎች በሙሉ
የወቅቱን የሃገራችንን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታ በማስመልከት ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !
” የምርጫ ውጤቱ ተቀባይነት የለውም። ድምፅ ተዘርፏል”
የስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተለይ የአዲስ አባባ የቅድመ ምርጫ ሂደት እና የድህረ ምርጫ የነጻ፣ የፍትሃዊነት እና የዴሞክራሲያዊ መመዘኛዎችን የማያሟላ መሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አስታውቋል።
“ገዥው ፓርቲ በዋና ፈፃሚነት፤ ምርጫ ቦርድ በተባባሪነት ዘርፈውታል። ይህም በመሆኑ በፍርድ ቤት ክስ መስርቻለው” ብሏል ፓርቲው ዛሬ ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የምርመራ ውጤት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የመጨረሻው የመራጮች ምዝገባ አሀዝ መሰረት በአዲስ አበባ 1.4 ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበዋል። ይኸው ቦርድ አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱን ይፋ ባደረገበት ዕለት እንዳስታወቀው ደግሞ በከተማዋ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ ሰጥተዋል። ይህም አራት መቶ ሺህ ዜጎች በምርጫ ቦርድ ሳይመዘገቡ መምረጣቸውን ያረጋግጣል። በመሆኑም ዝርፊያውን የራሱ የምርጫ ቦርድ ሪፖርት የሚያረጋግጥ መሆኑን ባልደራስ ጠቁሟል።
በአዲስ አበባ የቅድመ ምርጫ ሂደትን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ሰኔ 1ቀን 2013 ዓ.ም. በ25 ገጾች በተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት የእጩዎች፣ መራጮች እና የፓርቲ አባላት የደህንነት ሁኔታ፤ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የታዩ
መሰናክሎችን እና በምርጫ ቦርድ በኩል የታዩ ችግሮች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ፣ የመራጮች መዝገብባ እና የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን አስመልክቶ ከፍተኛ ችግር የነበረበት እና የምርጫ መመዘኛ ትንሹን መስፈርት ያላሟላ እንደነበር ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአዲስ አበባ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ሂደትን በተመለከተ ባልደራስ ያካሄደውን የጥናት ውጤት በዋናው ቢሮ በዛሬው ዕለት በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል ። የጥናት ውጤቱ በ30 ገጾች እና በ8 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። የሚከተሉትን አንኳር ጉዳዮችም ዳሷል፦
~ የድምፅ አሰጣጡን ስነ-ስርዓት እና የቆጠራ ሂደቱን
~ በድምፅ አሰጣጥ ሂደት በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ የታዩ ክፍተቶችን
~ የቅሬታ አፈታት
~ የፓርቲ ወኪሎች ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች
~የምርጫ አስፈፃሚዎች ማንነት እና ያሳዩዋቸው ተግባራት
~ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች የነበራቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ
~ በመራጮች ላይ የተፈጠሩ ጫናዎች
~ የምርጫ ጣቢያዎችን እና የምርጫ አዋጁን መቃኘት
በአጠቃላይ በድምፅ መስጫው ቀን እና በድህረ ምርጫው ቀናት የታዩ ህገ ወጥ ተግባራትን ዳሷል። መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ሳይናሳዊ እና አስረጂ በሆኑ የአጠናን ስልቶች አቅርቧል።
በምርጫው ጉዳይ ላይ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም የተደረገውን 6ኛ አገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ሂደት በተመለከተ መረጃዎችን በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የምርጫ ክልሎች በሙሉ በማሰባሰብ አጠናክሮ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ፣ በድምጽ አሰጣጡ እና ቆጠራው የነበሩ ችግሮችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ፓርቲያችን አቅርቦ ምላሽ በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አ/ቁ. 1162/11 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤትን ይፋ ከማድረጉ በፊት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ውጤቱን ከመግለጽ እንዲቆጠቡ የሚከለክል ሕጋዊ ድንጋጌ በመኖሩ ፓርቲያችን እስካሁን ለሕግ ተገዥ በመሆን በድምጽ መስጫ ቀን የነበሩትን ችግሮች እና ውጤቱን በሚመለከት መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቦ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ቦርዱ እስካሁን በተወሰኑ የአገራችን ክልሎች ያሉ ውጤቶችን ይፋ ከማድረጉ በስተቀር፣ በተሻለ መረጋጋት ውስጥ የተደረገውን የአዲስ አበባ ከተማን ውጤት አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ለህዝብ ይፋ ሳያደርግ ጊዜ እየወሰደ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
በፓርቲዎች የቀረቡ ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው፣ ቦርዱ ውጤቱን ያፋ ሳያደርግ በተድበሰበሰ ሁኔታ መቆየቱ አላስፈላጊ ለሆኑ እንቅስቃሴዎች በር የሚከፍት እንደሆነ ፓርቲያችን ይረዳል፡፡ አዲስ አበባን በተመለከተ በቦርዱ እጅ የገባው ውጤት የአንድ ፓርቲን የበላይነት እንደከዚህ በፊቱ የሚያረጋግጥ ሆነም አልሆነም፣ ፓርቲያችን እና ህዝቡ እውነቱን የማወቅ መብት አላቸው፡፡ ፓርቲያችን አሁንም የቦርዱን ሰብሳቢ፣ “ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የአዲስ አበባን ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ለመራጩ ህዝብ ይፋ ያድርጉ” ብሎ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ሆኖም፣ ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ ጊዜ አሁንም መውሰዱን የሚቀጥል ከሆነ፣ ፓርቲያችን በእጁ ያለውን የጥናት ሪፖርት ለህዝብ ይፋ ለማድረግ እና ለቀጣይ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት የሚገደድ ይሆናል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ።
ድል ለእውነተኛ ለዲሞክራሲ !!!
ኢትዮጵያ መቼ ይሆን ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚኖራት ?!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ፍትህ እንዲሰፍን ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ አድሎአዊነትና ዘረኝነት እንዲወገድ፣ሕዝብ ከመፈናቀልና ከድህነት እንዲላቀቀቅ፣ አዲስ አበባ የራስ ገዝ አስተዳደር እንድትሆን እና ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሰፍኑ የሚያስችል ሥርዓት ለማምጣት ጠንክሮ ሠርቷል፤እየሰራም ነው፡፡የሃገሪቱ መሪ ‹‹ከባልደራስ ጋር ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን›› እያሉ በተናገሩበት ወቅት እንኳን ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከመታገል ቁርጠኛ አቋሙ ወደ ኋላ አላለም፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በ6ኛው አገር አቀፍ ቅድመ ምርጫ ሂደት (Pre-election process) ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሳይንሳዊ ጥናቶች አካሂዶ ዝቅተኛውን ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት የማያሟላ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የምርጫ ሂደቱ የተበላሸ ከሆነ ውጤቱም በተመሳሳይ መንገድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ባልደራስ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲል በምርጫው የተሳተፈ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ፓርቲያችን ከአራት ወራት በፊት ጀምሮ ባካሄዳቸው ከፍተኛ የምርጫ እንቅስቃሴዎች ወቅት ሕዝብ ከጎኑ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አረጋግጧል፡፡አዲስ አበቤ ለድርጅታችን በአሳየው ደጀንነትም ፓርቲያችን እጅጉን ኮርቷል፡፡ ያነሳነውን አዲስ አበባን ራስ ገዝ የማድረግ ጉዞ ሕዝባችን ከጎናችን በመሆን ስለሰጠን ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ለሰጣችሁንም ድምፅ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህንኑ ወደ ፊትም አጠናክረን እንደምንሄድ በዚሁ አጋጣሚ እንገልፃለን ።
ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ገንዘባችሁንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ጭምር የለገሳችሁ የፓርቲው አመራሮች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች እጩዎች፣የምርጫው የቅስቀሳና የሎጂስቲክስ አካላት፣የባልደራስን የዴሞክራሲ ማዕዘን በመሆን የምርጫውን ሂደት ከሁለት ቀንና ሌሊት በላይ የተከታተላችሁ ወኪሎቻችን እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋና የምናቀርብላችሁ በታላቅ ደስታ ነው። በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በሌሎችም ዓለማት የምትኖሩ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድጋፍ ሰጭ ኮሚቴ እና የአማካሪ ቦርድ አባላት ላደረጋችሁት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ፣ ምክር እና አስተዋፆኦ ምስጋናችን እጅጉን ከፍ ያለ ነው፡፡
‹‹አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው›› በሚል ዓላማ የጀመርነውን ጉዞ ገዥው ፓርቲ መሪዎቻችንን በማሰር ለማሰናከል ጥረት አድርጓል፡፡ነገር ግን ትግሉ የተነሳበትን ዓላማ ይበልጥ ከፍ አድርጎ በመቀጠሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚገዙት ሃሳብ ሆኗል፡፡በሀገር ውስጥ ያላችሁ አባላት እና በውጭ ሃገር የምትኖሩ ድጋፍ ሰጭዎች የተሸረበውን ሴራ በጣጥሳችሁ በመውጣት፣ በሰላማዊ ትግሉ ፋና ወጊ የሆኑ መሪዎችን ቀንዲል ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረጋችሁ ናችሁና በድጋሚ የባልደራስ አመራር በእናንተ ደስታና ኩራት እንደሚሰማው ይገልጻል ።
በባልደራስ ፓርቲ ቅድመ ምርጫ ሂደት ጥናት እንደተረጋገጠው በብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ የታጀበው ዝቅተኛውን የምርጫ መመዘኛ ደረጃዎች ያላሟላው የሰኔ 14/2013 ዓ.ም. ምርጫ የመጣውን ውጤት ማሳየት ችሏል። እንደሌሎቹ ጊዜዎች ሁሉ የዘንድሮውንም ምርጫ ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከመንግሥት በኩል ምንም ቁርጠኝነት አለመኖሩን ፓርቲያችን ተገንዝቧል።
ከምርጫው ቀን ዋዜማ ጀምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ የፓሊስ እና የመከላከያ አባላት የጦር መሣሪያቸውን ወድረው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የስነ ልቦና ጫና ሲፈጥሩ ሰንብተዋል፡፡ ይህም ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ›› እንደሚባለው በምርጫው ሰሞን ከነበሩ ኢዲሞክራሲያዊ ትዕይንቶች አንዱ ነበር።
ምርጫውን ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ጠቀሜታው በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት እና ተወዳድረው ለማሸነፍ ለሚፎካከሩት ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለሚወክሉት ሕዝብ ጭምር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምርጫው ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ሲቀር የሕዝብ ነፃነት ይገፈፋል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡በዜጐች መካከል የደረጃ ልዩነት እና መሠል ችግሮች ተፈጥረው ህዝብ በፍርሃት አረንቋ ውስጥ ይወድቃል።እነዚህን ችግሮችን ለማስወገድ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ሓላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የተከሰቱ ችግሮችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጥልቀት እየመረመረው ይገኛል። እስካሁን በደረሰበት ሁኔታ ምርጫው ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ተግባራት መኖራቸውን ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ለአብነትም፡-
1. ድምፅ አሰጣጥንበ በተመለከተ ግንዛቤ ለመስጠት የተሰየሙት የምርጫ አስፈፃሚዎች የገዢው ፓርቲ እንዲመረጥ የሚረዳ ገለጻ ሲያካሂዱ የፓርቲዎች ወኪሎች እርምት እንዲያደርጉ ቢያስገነዝቡም አስፈፃሚዎች ብልሹ አሠራራቸውን አለማስተካከላቸው በችግርነት የታየ ጉዳይ ነው፡፡
2. በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያልነበሩ አዳዲስ ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ከመክፈት በተጨማሪ ማንነታቸው የማይታወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ሲሰጡባቸው መቆየታቸው፣
3. አቅመ ደካሞችን፣ በእድሜ የገፉትን እና የአካል ጉዳተኞችን የመንግሥት ካድሬዎች ከምርጫ ህጉ ውጭ በማገዝ ስም በሚስጥር ድምፅ በሚሰጥባቸው ክፍሎች ይዘዋቸው በመግባት ጫና እየፈጠሩ የሚፈልጉትን ማስመረጣቸው፣
4. በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የባልደራስን የምርጫ ውጤት ቁጥሮች እየቀነሱ እንዲጻፉ መደረጋቸው፣
5. ባልደራስ የተመረጠባቸውን ወረቀቶች በስልት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ወይም የባከኑ ውጤቶች እንዲሆኑ መደረጋቸው፣
6. በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ያለው የመራጩ ቁጥር ቀድሞ የሚታወቅ ሆኖ እያለ በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከመራጮች ቁጥር እንዲያንስ መደረጉና ወረቀቱ እስኪመጣ መራጮች በፀሀይ፣ በዝናብና በብርድ በርካታ ሠዓታት እንዲቆዩ መሆናቸው የተወሰኑት ሳይመርጡ ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል፡፡
7. ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች በርካታ በመሆናቸውና በምርጫ ወረቀቱ ላይ በምርጫ አስፈፃሚዎች በቂ እና ግልጽ ማብራሪያ ባለመሰጠቱ የምርጫ ወረቀቱ በውስጡ ምን ያህል እጩዎች እንደያዘ አለመታወቁ ለመራጮች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥር ሆኗል፡፡ይህም መራጩ በግልጽ ድምፅ የመስጠት ነፃነት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡በዚህም የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዲባክኑ ወይም መራጩ ላልፈለገው ድምፅ እንዲሰጥ ሆኗል፡፡ከላይ የተጠቀሱት በምሳሌነት ከሚነሱት ችግሮች እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ለችግረኛ ሰዎች የተለያዩ መደለያዎች በመስጠት የሕዝብን ገንዘብ ለሥልጣን መሸመቻ ማድረጉ በምድር ቀርቶ በፈጣሪ ዘንድ ይቅር የማያሰኝ ተግባር ነው። በሌሎች ጊዜዎች የድሆችን ችግር ለማስወገድ ትኩረት የማይሰጠው ገዥው ፓርቲ በምርጫ ሠዓት ብቻ ማባበያ ይዞ መቅረቡ ነዋሪውን ለመደገፍ ሳይሆን ሥልጣኑን ለማቆየት የተጠቀመበት ዘዴ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ከምርጫ 97 ወዲህ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲበዙ የተደረገባቸው ምክንያቶች ኗሪዎች በረጃጅም ሰልፎች ላይ በመቆየት እንዳይንገላቱ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ምርጫ ጣቢያዎች እንደአሸን እንዲፈሉ በተደረገበት ወቅት መራጮችን ለማሰላቸትና ለማስመረር ይሁን ተብሎ የተከናወኑት ማጓተቶች ድምፅ ሰጭዎች እንዲንገላቱ ማድረጉ የሚያስተዛዝብ ሁኔታን ፈጥሯል። ቀን በፀሀይና በዝናብ፣ በምሽት እና በሌሊት ደግሞ በብርድ እንዲንገላታ የተደረገበትን ደባ ተቋቁሞ የተሰለፈው አዲስ አበቤ ድምፁን ለማን እንደሰጠ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠንቅቆ ያውቃል ።
በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ለማሰላቸት ሆን ተብሎ በተፈጠረው ተስፋ የማስቆረጥ ሂደት ሳትመርጡ ለቀራችሁ፣ ሆን ተብሎ በተሠራ ደባ ካርድ እንዳታወጡ የተደረጋችሁ እና መምረጥ ያልቻላችሁ፣ ጊዜ በማጣት ካርድ ላልወሰዳችሁ፣እንዲሁም በአገራችን ሁኔታ ተስፋ በመቁረጥ የዜግነት ግዴታ መወጣት ያልቻላችሁ የናንተ ድምፅ ሀገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግሮች መውጫ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሆኖ ሳለ በመቅረቱ በእጅጉ ያስቆጫል።
የአሁኑ የኦህዴድ/ብልጽግና አባት የሆነው ህውሃት/ኢህአዴግ በምርጫ 2007 የ100% የአሸነፍኩ ጉዞ ከ2ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት እንዳልቻለ የ3 ዓመት ትውስታችን ነው።በህዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ራሱን ይሸነግል ይሆናል እንጂ ረጅም ርቀት እንደማይጓዝ ከዚሁ ከሀገራችን ታሪክ መረዳት ይቻላል። ለነፃ፣ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዳኝነት የሚሰጠው ሕዝብ ነውና።
6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ‹‹ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አደርጋለሁ›› ይል የነበረው ኦህዴድ/ብልጽግና በምርጫው ዙሪያ እየተፈጸሙ ያሉት ድርጊቶች የማያልቅ ሀሰቱ ማሳያዎች ሆነዋል። ዜጎች እየተገደሉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እየተጣሰ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ እየተራቡ እና እየተደፈሩ፣የውጭ ወራሪ ኃይሎች ድንበር ጥሰው ሀገራችን ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ እየሆኑ ‹‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል፡፡ … ›› የተሰኙት አባባሎች ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ከማለት ያለፈ ትርጉም የላቸውም።
የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰጠን ታላቅ ድጋፍና ፍቅር፣ ክብርና ሞገስ አሁንም ደግመን እናመሰግነዋለን። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች እና አባላት በሕዝብ ፊት በተግባር ጭምር እየተፈተንን የሰላማዊ ትግል አርበኞች መሆናችንን አስመስክረናል፡፡
የዴሞክራሲ ኃይሎች ትንንሽ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለማይቀረው የሰላማዊ ትግል ተደጋግፈን ሕዝብን በማስተባበር እንድንታገል ዛሬም እንደቀድሞው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል።
ብሔራዊ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም. የተካሄደወን የምርጫ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ባልደራስ መግለጫ የሚሰጥ መሆኑን በአክብሮት ይገልጻል፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ!!!
ሰኔ 18/2013ዓ.ም.
የባልደራስ የምርጫ ዘመቻ ዝግጅት ማብቂያ ፕሮግራም ላይ የተደረገ ንግግር
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ባለፉት አራት ወራት የቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴው በሃራዊ እና በአዲስ አበባ ነክ ጉዳዮች ፓርቲው የሚያራምደውን ፖሊሲዎች ለከተማው ሕዝብ በተለያዩ መድረኮች እና የቅስቀሳ ዜዴዎች ለማሳገንዘብ ጥረት ሲደርግ ቆይቷል፡፡
በሃገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለውን አመለካከት በሃገር አቀፍ ማኒፌስቶው አስፎሮ አሰራጭቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ሕዝብ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም በሚካሄደው ምርጫ ቢመርጠው፣ ስር የሰደዱ የከተማይቱን ችግሮች ለመፍታት የነደፋቸውን ፖሊሲዎች ደግሞ በአዲስ አበባ ማኒፌስቶው አማካይነት በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በዛሬው የቅድመ ምርጫ የባልደራስን የምረጡን ቅስቀሳ መርሃግብር መጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ ፓቲያችን ባልደራስ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ለማስገንዘብ የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ለየት ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህም ጉዳዮች ፓርቲችን ባልደራስ በተመለከተ በኦህዴድ/ብልፅግና በገሃድ ጥብቅና በቆሙለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በስውር እየተነዛብ ያለውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ምንነት ይፋ በማውጣት ባልደራስ የማይወክሉ መሆናቸውን አስረግጠን ለማቅረብ ነው፡፡
1ኛ/ አዲስ አበባን በተመለከተ በመርህ ደረጃ ልዩ ጥቅም አራማጆች ጋር በመርህ ደረጃ የማንስማማ መሆኑን፣ በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል አንዱ ጥቅም ሰጭ፣ አንዱ ጥቅም ተቀባይ እንዲሆን መፈለጉ ህጋዊም ዲሞክራሲያዊም አይደለም የሚለው አቋማችን ለምን ጊዜም አይቀየርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አባባል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተቱ አግባብ አለመሆኑን ደጋግመን ገልፀናል፡፡ ሕገ መንግስቱም በሕዝብ ይሁንታ እንዲቀየር ለሪፈረንደም እንዲቀርብ በሰላማዊ መንገድ የምንታገልለት የፀና አቋማችን ነው፡፡
ይህ አቋማችንን የማይቀበለው የኦሮሞ ሕዝብ ሳይሆን የነገድ ፓለቲካ አራማጆች የሆኑ የኦሮሙማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎቱ ከሌሎች ወንድም ከሆኑ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ጋር በአንድ ሃገር ሕዝብነት ሰሜት በሰላም፣ በእኩልነት እና በወንድማማችነት የጋራ ሃገራችንን ኢትዮጵያን እያለማ የጋራ ተጠቃሚ ሆኖ መኖርን እንደሆነ እንዳችም ጥርጥር የለንም፡፡ ይሁንና የማንነት ፖለቲካን ካላራመዱ የሕዝብ ድጋፍ እንደማያገኙ የተራዱ የኦሮሞ ፅንፈኛ የነገድ ፖለቲከኞች ባልደራስ የኦሮሞን ሕዝብ እንደሚጠላ በማስመሰል ፓርቲያችን ላይ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛብን ቆይቷል፡፡ ባልደራስ ኦሮሞ ማበረሰብ ጋር አንዳችም ጠብ የለውም፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የተለዩ ጥቅም ይሰጠኝ ብሎ ጠይቆ እንደማያውቅ፣ ይህን ጥያቄ የሚያራግቡት ፅንፈኛ ብሄርተኞች ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከእነሱም ጋር ቢሆን ፓርቲያችን ባልደራስ ከተመሰረተ ጀምሮ እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው የሚታገለው በሰላማዊ መንገድ እና በሰላማዊ የፖለቲካ ዘይቤ ብቻ ነው፡፡ ባልደራስ የሚያራምደው የፖለቲካ አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች በጋራ ጥቅም መርሆች አማካይነት በሰላም አብረው እንደኖሩት በዚያው መልክ እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ፖለቲካን በሰለጠነ፣ በዘመነ፣ በፀብ ሳይሆን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ልዩነት መፍታት የሚቀበል ይህን አካሂድ ብቻ የሚያራምድ የፖለቲካ የተከተለ ነው፡፡
የኦሮሞ ማህበረሰብን ጨምሮ ሌሎችንም በርካታ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ዘላቂና መሰረታዊ ጥቅም የሚከበረው በሰላማዊ መንገድ እንጅ በፀብ እና በብጥብጥ እንዳልሆነ ፓርቲያችን ባልደራስ የፀና እና የማይናጋ አቋም አለው፡፡
ሌላው በፓርተያችን ላይ የብልፅግና ፓርቲ በጥቅም በመግዛት በደጋፊነት ባሰማራቸው የኢትዮጵያ ሙስሊም በማይወክሉ ብድኖች ባልደራስ ፀረ- እስላም ነው እሉ ስለሚያስነዙት የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ ባልደራስ እንደሌሎች ፅንፈኛ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ታሪክ ትርክት ሰለባ አይደለም፡፡ ባልደራስ ጥንታዊ ሃገራችን ኢትዮጵያ የአብርሃም ኃይማኖቶች የሆኑት የክርስትና የእስልምና እና የአይሁድ ኃይማኖቶች ጥንታዊ መዳረሻ እንደሆነች ይቀበላል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እነዚህ ኃይማቶች ከመነጩበት ከመካከለኛው ምስራቅ ብትወርስም ከራሷ ባህልና ልማድ ጋር አዋህዳ፣ ወዝና ጠረኗን በውስጣቸው አስርጻ ፍፁም ሀገራዊ እምነቶች እንዲሆኑ አድርጋ ኮትኩታ በማሳደግ በህዝቡ ውስጥ ስር እንዲሰዱ አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገሮች ቀድማ እነዚህን ወንድማማች የአብርሃም ኃይማኖቶች ሀገራዊ ቅርፅና መገለጫ እንዲኖራቸው አድርጋ ያቆየቻቸው ኃይማኖቶች በመሆናቸው ፓርቲያችን ባልደራስ በኢትዮጵያ ክርስትና እና በኢትዮጵያ እስልምና መካከል አድሏዊ ፖለቲካ አይከተልም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ታላላቅ ኃይማኖቶች የሚያራምዷቸው እምነቶች ከኢትዮጵያ ልዩ ሀገራዊ ባህሪ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ፓርቲያችን ያለማወላወል ይቀበላል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሃገራችን ያለው ሕዝብ የተቀበላቸው ኃይማኖቶች በእውነተኛ እኩልነት እና ነፃነት እምነታቸውን ማራመድ፣ የእምነት ጉዳዮቻቸውን አለ መንግስት እና ፖለቲካ ተፅእኖ፣ ጫና፣ አድሏዊ እና ጣልቃ ገብነት ሳይደረግ በራሳቸው በአማኞችና አማኞች በነፃነት በሚቀበሉት አመራር ብቻ እየተመራ ሊከናውን ይገባል የሚል ፅኑ እና የማይናወጥ አቋም አለው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቢመርጠውም በማናቸውም ሁኔታ ሳያዛንፍ ተግባራዊ የሚያደርገው ይህንኑ አቋሙን እንደሆነ ለክርስትና እና ለእስልምና ቤተ እምነቶች እና ለምእመናኖዎቻቸው ለማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ለማስገንዘብ የሚፈልገው ሰላምን ወንድማማችነት፣ እውነትን፣ ለጋስነትን፣ ከሚያስተምር ቂምና ጥላቻን፣ ራስ ወዳድነትን የሚያወግዝ ኃይማኖታዊ አስተምህሮን የሚከተል ወገናችን ከሆነው ሕዝብ ሙስሊም ጋር በፍቅር እና በሰላም እና የአንድ ሃገር ልጅነትን አብሮ መኖርን እንጅ ምንም ዓይነት የጥላቻ አመለካከት የማናራምድ መሆናችንን እንዲገነዘብልን እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ውጭ አንድ እምነትን የሚያገል አመለካከት ለሀገር ሰላም ጠንቅ መሆኑን ጠንቅቆ የሚገነዘብ ፓርቲ ነው፡፡
በፓርቲያችን ላይ የሚነዛው ሌላው ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ደግሞ ባልደራስ በአዲስ አበባ ህዝብ ቢመረጥ የብልፅግና አባል የነበሩ የከተማው መስተዳድር ሠራተኞችን ከሥራ ያባርራል እየተባለ የሚነዛው የሃሰት ወሬ ነው፡፡ ባልደራስ በከተማው ቢመረጥ የብልፅግና አባል የሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን ማባረሩን ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡ የፓርቲ አባልነታቸውን እንደጠበቁ የመንግሥት ሥራ መበስራት እንዲቀጥሉ እናደርጋለን፡፡
ሌላው በፓርቲያችን ላይ እየተነዛ ያለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ባልደራስ በፀብ እና በፍጥጫ የሚያምን ፓርቲ ነው ስለሚባለው ነው፡፡ ባልደራስ የሚያራምዳቸውን የፖለቲካ አመለካከቶች በደም ፍላት እና በስሜት የተቀበላቸው አመለካከቶች አይደሉም፡፡ አውጥቶ አውርዶ፣ መክሮ እና አስመክሮ፤ በሰነድነት ሰንዶ ለሃገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ እና ለአዲስ አበባ ሕዝብ በተለይ ይበጃሉ ብሎ የተቀበላቸውን ነው፡፡ ባልደራስ ከፀብ እና ከፍጥጫ ሃገራችን ኢትዮጵያም ሆነች የሁላችንም ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ይጠቀማሉ ብሎ ለአንድ ደቂቃም አምኖ አያውቅም፡፡ በዚያው ልክ ተረኝነትን፣ አድርባይነትን፣ ተቅለስላሽነትን ይፀይፋል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ እውነትን እውነት፣ ሃሰትን ሃሰትን ነው ብሎ በይፋ መቆምን እንደ ትክክለኛ መርህ አድርጎ ይቀበላል፡፡
ልዩነት በገሃድ እውጥቶ በፀብ አጫሪነት ሳይሆን በውይይት መፍታትን፣ በውይይት የማይፈታ ነገርን በማሳደርና መልሶ ለውይይት በማቅረብ፣ በዚያም መልኩ ካልተፈታ በሰላማዊ መንገድ በሪፈረንደም በህዝብ ዳኝነት እንዲፈቱ ለማድረግ በፅናት የሚታገል ፓርቲ ነው፡፡ በማጎብደድ የሃገር እና የሕዝብ ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለውም፡፡ አሁን እየታዩ እንዳለው አካፋን አካፋ ማለት ካልተቻለ ሀገር እና ህዝብን ወደ አስከፊ ሁኔታ እየተመራ እንደሆነ ማስገንዘቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ፓርቲችን በዚህ አጋጣ ሃገራችን ለገባችበት ሁለንተናዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስ መፍትሄው በመንግስት እና በአጋሮቹ ፍላጎት ብቻ በተፅእኖ የሚገፋው “ብሄራዊነት” የሌለው ምርጫ ሳይሆን አካታች በመሆኑ መልኩ የሚጠራ እና የሚካሄድ ብሔራዊ ውይይት እንደሆነ ፅኑ እምነት አለው፡፡፡፡
በዚህ አጋጣሚ ወንድም በሆነው የትግራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ፣ ጦርነቱ ተሳታፊ ባልሆኑ ዜጎች ላይ በሃገር መከላከያ አባላትና በኤርትራ ጦር እየደረሰ ያለውን ጥቃት፣ በክልሉ ሴት እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን የፆታዊ መደፈር ፓርቲችን ባልደራስ በፅኑ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ባልደራስ በፅኑ ያወግዛል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ በትግራ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ የፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ ፍልሚያ ተከትሎ በአካባቢው እያንዣበበ ያለው የርሃብ አደጋ ህዝቡን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑን ስለሚገነዘብ በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ የሕወሓት ተልእኮ ተሸካሚ ያልሆኑ የትግራ ልሂቃን ከአማራው የፖለቲካ ልሂቃን እና ከሌሎች ሃገራዊ ኃይሎች ጋር በመገናኘት የድህረ ሕወሓት የግትራይ የፖለቲካ ቀውስ ስለሚፈታበት ሁኔታ ምክክር እንዲደርጉ ፓርቲያችን ለሚመለከታቸው የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኢትዮጵያ ከሃያላን ምዕራባውያን ጋር የገባችበትን የሃገራዊ ግንኙነት ቀውስ በተመለከተ የፓርቲያችን የባልደራስ አመለካከት ግልፅ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ በቅድሚ የአባይ ወንዝ መገደብ ለኢትዮጵያ ልማት ቁልፍ ግብዓት መሆኑን ፓርቲችን ያምናል፡፡ በመሆኑም የብልፅግና መንግስት እየተዘጋጀበት ያለውን የግድቡን ሁለተኛ ሙሌት በታቀደለት ፕሮግራም መሰረት መሞላቱን ፓርቲያችንን ባልደራስ በፅኑ የሚደግፍ ሲሆን፣ ይህን አስመልክቶ ምዕራባዊያን ሃያላን ሀገሮች የሚያራምዱትን ለግብፅ እና ለሱዳን ያዳላ አቋም ፓርችን በፅናት ይቃወመዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰሜን ምዐራብ ድንበር በወራሪ የሰሜን የሱዳን ሠራዊት ተጥሶ እና ስፋት ያለው የሃገራችን ሉዓላዊ ግዛት ተወሮ ባለበት ሁኔታ፣ ይህን ወረራ ለመቀልበስና የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ለማስመለስ አንዳችም ተጨባጭ እርምጃ ሲወስድ የማይታየው የብልፅግና መንግሥት ምዕራባውያን ሃያላን ሀገሮች ባለሥልጣኖች ላይ ያደረጉትን የጉዞ ማዕቀብ እና ቀድሞውንም የሚታወቀውን የህወሓት ደጋፊነታቸውን በማጣቀስ የሃገራችን ሉዓላዊነት እንደተደፈረ አድርጎ የሚያቀርበው ፕሮፖጋንዳ አሳዛኝ ነው፡፡ የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ እንዲቆይ መደረጉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ መሆኑን ለማድበስበስ ይፈልጋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ፓርቲያችን ባልደራስ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃገሮች መሆናቸውን ቢገነዘብም፣ በሁለቱም ሀገሮች ያለው ህዝብ በኃይማኖት፣ በቋንቋ በባህል እና በፌደል ሳቀር የተሰናሰለ አንድ ህዝብ መሆኑን ያምናል፡፡ ቀደም ሲል ወደ መለያየት ያመሩ ምክንያቶች ታርመው፣ የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት በወታደራዊ ጉዳዮች ከመረዳዳት በዘለለ ወደ ስርዓት መነግስታት ጥምረትነት ደረጃ ከፍ እንዲል ቢደረግ ለሁለቱም ሃገሮች ሕዝብ ይጠቅማል የሚል የፀና አመለካከት አለው፡፡
በመጨረሻም ባልደራስ 6ኛውን የምርጫ የሀገራችን ህዝቦች በታሪካቸው በድምፃቸው መንግሥትን የሚመርጡበት፣ የህዝብ ድምፅ በትክክል የሚከበርበት እንዲሆን ፓርቲያችን ይመኛል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ገዥው ፓርቲ ጨምሮ ለነፃ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን በትህትና እናቀርባለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ
ድል ለዲሞክራሲ!!!