ዜና
Balderas Latest News
የሃዘን መግለጫ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአሜሪካን የባልደራስ ደጋፊ የነበሩትን ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወዬሳን ድንገተኛ ሞት ሲሰማ ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶታል። አቶ ዳዊት ከበደ በጋዜጠኝነት ሙያ ለረጅም ጊዜ ሀገራቸውን በቅንነት ያገለገሉ ከመሆኑም ባሻገር ሙያቸውን አክባሪ፣ ትሁትና ቅን ሰው ወዳድ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው።
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የፓርቲያችን መሥራችና ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከጀግናው እስክንድር ነጋ ጋር የነበራቸው ሙያዊ ግንኙነትና ወንድማዊ ቀረቤታ ለብዙዎቻችን የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች የሚሰማንን ሀዘን የበለጠ የመረረ ያደርገዋል።ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የተሰማውን መሪር ሀዘን እየገለፀ ለመላው ቤተሰባቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
የትግል አጋራችን የነበሩትን የወንድማችን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን!
በባልደራስ ስም ሃክ በተደረጉ የፌስቡክ አካውንቶች የሃሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የባልደራስ ሥ/አስፈጻሚ አስጠነቀቀ
ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከ60 በላይ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ለቤተመንግስት ማስፋፊያ በሚል በመንግስት ሀይሎች መፍረሳቸው ተነገረ
ህመሙ _አመመኝ
አቶ ስንታየሁ ቸኮል የኅሊና እስረኛ ከቂሊንጦ
እስክንድር ነጋ የድርጅቴ መሪ ራስ ነው!
ለኔ ደግሞ የሥራ አለቃዬ ነው!
እስክንድር ታላቅ ወንድሜ መካሪዬ ነው።
እስክንድር ለጋራ መስዋዕትነት የተጠራን የቁርጥ ቀን የሀገሬ ሕብረ_ቀለም ሃቀኛ ጓዴ ነው።
ከመሪዬ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ሆነን በተቀራረበ መኝታ ላይ እንዴት እንዳዳረ አውቃለሁ። ህመሙ- አመመኝ… ላብ በሚያጠምቅ ምጥ ..እእእእእ… የጥዝጣዜ ስሜት ቦታው ላይ መፍትሄ አጥተህ መጋራት ከባድ ነው። ቁጭት የተቀላቀለበት ህመም ብስጭት መራር ሀዘን ብቻ ያሳዝናል።
ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ,ም ጠዋት 1:00 ሰዓት ላይ እስክንድር እንደወትሮው ወደ ውጭ እያነከሰ ወጣ እንዴት እንዳደረ ስሜቱን አውቃለሁ፤ “ለምን ትወጣለህ ተኛ እንጅ እስክንድር” አልኩት። ለሊቱን ሙሉ እንዳልተኛ እና እግሩ በጣም እንዳመመው ነገረኝ። ይህን እኔም ስለሰማሁት ወዲያው በሙቅ ውሃ ለማሸት ሞከርኩ ግን ብዙም አልተቻለም። እጅግ የከፋ ህመሙ ተሰምቶት ነበር። በአስቸኳይ ወደ እክምና እንዲሄድ ለተረኛ ፖሊስ መኮንን ተናገረ.. ወደ ፖሊስ በመሄድ የእስክንድር እግር መሰበሩ በህክምና ተነገረው ።
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በሥርዓቱ ዕቅድና ተልዕኮ የተደበደበው እስክንድር ነጋ፣ ዛሬ ከሰዓት ቦኃላ በፖሊስ ሆስፒታል በተደረገለት ህክምና ፣ በግራ እግሩ ላይ አውራ ጣቱ መሰበሩ በራጂ ታውቋል።
በዚህም መሠረት፣ ለሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት የሚቆይ ጄሶ ተደርጎለታል እንደሚቆይ ተነግሮታል።
ጠንካራው መሪያችን እስክንድር ነጋ ከማረሚያ ቤት ሆኖ ያስተላለፈው መልዕክት፣ ስሜት ቀስቃሽ ወኔ የሚጠግን ነበር።
“…በሰሜን ያለውን ጦርነት አስባለሁ። የታሰሩትን አባሎቻችንን አስባለሁ። አጥንታችንን መስበር ይቻላል። ትግላችንን ግን መስበር አይቻልም ” ብሏል።
ወኔ ያለው አመራር ይህ ነው። እስክንድር ነፍሱ ለእውነት የተጠራች ጀግና ታጋይ ነው። አምላኩን ሁሌም የማይረሳ በችግር ላይ ሆኖ ስለፍቅር ይቅርታ የሚሰብክ ደቀመዝሙር ነው።
የኛን ችሎት ለመታደም የመጡ የባልደራስ ፈርጦቻችን እናተ በርቱዎች በመስዋዕትነታችሁ ኮርተናል በመከራችሁ ብናዝንም ይህ እስራችሁ ግን ተመንዝሮ ህዝብ ይከፍላችዋል። ታሪክ ይክሳችዋል! ስለእኛ ዋጋ የምትከፍሉ ስለሀገራችሁ መፃሂ ዕድል ዛሬ በቆራጥ ትግል ያላችሁ ጓዶች ሁሉ እመነኙ ህዝብ አይረሳችሁም ከዚች ጠባብ እስር ቤት ሆነን እናስባችዋለን እናከብራችዋለን።
ድል ህዝባችን!
ድል ለሃቀኛ ታጋዮች!
የእስክንድር እግር መሰበሩ በህክምና ተረጋገጠ !
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በዕቅድ የተደበደበው እስክንድር ነጋ፣ ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በፖሊስ ሆስፒታል በተደረገለት ህክምና ፣ በግራ እግሩ ላይ ያለው አውራ ጣቱ መሰበሩ በራጂ ተረጋግጧል።
በዚህም መሠረት፣ ለሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት የሚቆይ ጄሶ ተደርጎለታል።
እስክንድር ከማረሚያ ቤት ሆኖ ባስተላለፈው መልዕክት፣ “በሰሜን ያለውን ጦርነት አስባለሁ። የታሰሩትን አባሎቻችንን አስባለሁ። አጥንታችንን መስበር ይቻላል። ትግላችንን ግን መስበር አይቻልም ” ብሏል።
በጅምላ ከታሰሩት መካከል ሁለቱ በዋስ ሲለቀቁ 40ዎቹ ለሰኞ ተቀጠሩ !
የእነ እስክንድር ነጋን የችሎት ውሎ ለመታደም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በጥቅምት 11/2014 ዓ/ም የሄዱ 42 የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በትላንትናው ዕለት በፓሊስ ታፍሰው መታሰራቸው ይታወቃል።
አቶ እስክንድር በእስር ቤት የደረሰባቸውን ድብደባ በችሎት የሰሙ ታዳሚዎች እያለቀሱ ችሎቱን አቋርጠው የወጡ ሲሆን ፤ ከችሎት ወጥተው በመንገድ ላይ ፖሊስ በጅምላ አፍሶ በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ቆይተው ፤ ምሽት አንድ ሰዓት ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ታስረው ነበር። ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
ፖሊስ በዛሬው ችሎት እንደገለጸው ተጠርጣሪዎቹ ” ችሎት ውስጥ ረብሸዋል፣ ሲወጡ ደግሞ ፍትህ የለም ፣ መንግስት የለም በማለት ሁከት እና ብጥብጥ በመቀስቀስ ” ሲንቀሳቀሱ መያዙን ገልጿል ። ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ የምስክሮችን ቃለ ለመቀበል እና ማስረጃቸውን ለማሰባሰብ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ቆጠሮ ጠይቋል።
የ42ቱ ተጠርጣሪዎች ጠበቆች ፖሊስ ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ አቤቱታ ውድቅ እንዲሆን በመጠየቅ ፤ ” በችሎት ውስጥ ተፈጸመ ለተባለው ድርጊት ፖሊስ የሚመለከተው ሳይሆን በወቅቱ ችሎቱ በራሱ ትዕዛዝ የሚሰጥበት ነው። ሆኖም ግን ችሎቱ ምንም አይነት ትዕዛዝ ባልሰጠበት ፖሊስ ያቀረበው አቤቱታ ተገቢ አይደለም” ብለዋል ።
ከዚህም በተጨማሪ ” ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀበት ምክንያት በሕግ ምንም አይነት ድጋፍ ” የለውም በማለት የጊዜ ቀጠሮው ውድቅ እንዲሆን በመጠየቅ ከእስር እንዲለቀቁ ለፍ/ቤት ጥያቄ አቅርበዋል ።
ግራና ቀኙን ያከራከረው ፍርድ ቤት ሁለት ህፃናት ልጆች ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በዋስትና እንዲወጡ፣ የተቀሩትን ደግሞ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ወደ 3 ቀን በመቀየር ለፊታችን ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲቀርቡ፣ እንዲሁም የተጠርጣሪዎቹን ተሳትፎ ለይቶ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ።
እስረኞች በተያዙበት ወቅት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ችሎቱም ለደረሰባቸው ጥሰት ክስ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጿል ።
በጅምላ ከታሰሩት መካከል ሁለቱ በዋስ ሲለቀቁ 40ዎቹ ለሰኞ ተቀጠሩ !
በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን!!!
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ በሚኖሩበት ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ውስጥ ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም. ንጋት 12፡20 ደቂቃ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ከአቶ እስክንድር ነጋ ጋር አብረው በእስር ላይ ያሉት የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተገኙ ሲሆን የባልደራስ ፕሬዘዳንት ወህኒ ቤት ውስጥ በተደራጀ የውንብድና ቡድን መደብደባቸውን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያትም አቶ እስክንድር ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ከችሎት መልስ የአቶ እስክንድር ጠበቆች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የባልደራስ አመራሮችና አባላት ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሄደው ለመጠየቅ ቢሞክሩም አቶ እስክንድር ከታሰሩበት ክፍል ወጥተው ማነጋገር አልቻሉም። ሆኖም በተፈጸመባቸው ድብደባ ግንባራቸው፣ ዓይናቸው አካባቢ እና ጉልበታቸው ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ፓርቲያችን አረጋግጧል። ነገር ግን ለደረሰባቸው ጉዳት የተደረገላቸው ህክምና አለመኖሩም ታውቋል። ስለዚህ በአስቸኳይ ቤተሰቦቻቸው ወደ መረጡት ሆስፒታል ተወስደው እንዲታከሙ እንጠይቃለን።
ድብደባው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና መሥሪያ ቤቱን በቀጥታ በሚቆጣጠረው ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሊፈጸም እንደቻለ መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። ይህም የኅሊና እስረኞችን በተለይም የአቶ እስክንድር ነጋን ህይወት ለመቅጠፍ የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ ማለማመጃ ምዕራፍ እንደሆነ ባልደራስ ይረዳል። በመሆኑም ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቀጥታ ለሕዝብ መግለጫ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
ፓርቲያችን ይህንን የሚለው አቶ እስክንድር ነጋ ከዚህ በፊት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በቃሊቲ ወህኒ ቤት እንዲሁም ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በወታደር ቁጥጥር ስር በዋሉበት ጊዜ እና ቢሯቸው ውስጥ የደረሱባቸውን በመጠን የተለያዩ ድብደባዎች ሁሉ በማስታወስ ነው።
ከዚህ ጋ በተያያዘም ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም. በነአቶ እስክንድር ነጋ የፍርድ ሂደት ችሎት ታድመው የነበሩ 42 የፓርቲያችን አባላት ታፍሰው ልደታ ክፍለ ከተማ የፖሊስ መምሪያ ከቆዩ በኋላ አመሻሹ ላይ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው እንዲታሠሩ ተደርገዋል። ከታሠሩት ውስጥ 12ቱ ሴቶች መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የታሠሩት አባሎቹ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ይጠይቃል።
ድል ለዴሞክራሲ!!!
መረጃ ! በእስክንድር ነጋ ላይ በማረሚያ ቤት ድብደባ ተፈጽሞበታል
በእስክንድር ነጋ ላይ በማረሚያ ቤት ድብደባ ተፈጽሞበታል ። በዚህም ምክንያት ጉልበቱ መቁሰሉን ዋና ሳጅን መስፍን ይልማ የተባሉ የቂሊንጦ ወህኒ ቤት የፈረቃ ሓላፊ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል! በዛሬው ዕለት እስክንድር ነጋ ችሎት መቅረብ አልቻለም ።
ይህም በመሆኑ በተከታታይ ምስክር የመስማት ቀጠሮ ተሰርዞ ፤ ለፊታችን ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ተዘዋውሯል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችሎት ለመታደም የተገኙ በጅምላ ታፍሰው ልደታ ፖሊስ ጣቢያ መምሪያ ተወስደዋል ።
አጠቃላይ ዝርዝር መረጃዎችን ወደኋላ እንመለስበታለን።