የባልደራስ አመሠራረት 

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በአዲስ አበባ ደረጃ የተቋቋመ የመጀመሪያው ‘ክልላዊ’ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ቀኝ ዘመም (Center to right) ፓርቲም ነው።

ባልደራስ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀቀኛው ጋዜጠኛ እና በፅኑው የሰብዓዊ መብቶች ታጋይ በአቶ እስክንድር ነጋ መሪነት በጎዳና ላይ ተመሰረተ። የግል ኩባንያ ከሆነው ኢንተርኮንቲነታል ሆቴል በዘጠና ሺህ ብር የተከራየውን የስብሰባ አዳራሽ በአምባገነኑ መንግሥት ተከልክሎ ጎዳና ላይ ቅድመ መሥራች ጉባኤውን በማድረግ አቶ እስክንድር ነጋን ፕሬዚደንቱ አድርጎ መርጦ የተመሠረተ ፓርቲ ነው። ቀጥሎም የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ.ኢ.አ.ድ.) ዋና ፅህፈት ቤት በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ እስክንድር ነጋ በቃለ መሀላ ስነ ስርዓት መሪነታቸውን ተቀብለዋል። የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትም ተመርጠዋል።
ለዚህ ፓርቲ መሰረቱ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባልደራስ አዳራሽ የተመሠረተው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ነው። ባለ አደራ ምክር ቤቱ አላማው የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ሳይሆን ፖለቲካውን የሚገራ የሲቪክ ተቋም ሆኖ የመቀጠል ፍላጎት ቢኖረውም በመንግሥት ክልከላ ሳይሳካ ቀርቷል። ቀጥሎም ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት መጣ።

በባልደራስ እምነት መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይባላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ባለሙሉ ሥልጣን ነው። ሀገሪቱን የማስተዳደር ሥልጣን ከሕዝብ ይመነጫል።

ባልደራስ ፕሬዚደንታዊ የመንግሥት አወቃቀር እንዲኖር ይታገላል። በፌዴራል መንግሥቱ ሥር የክፍላተ ሀገር መሥተዳድሮች እንዲኖሩም ይሻል። አብዛኛው የሥልጣን ክፍፍል ለፌዴራል መንግሥቱ መሰጠት አንዳለበት ያምናል። አዲስ በሚዘጋጀው ሕገ መንግሥትም የክፍለ ሀገር መስተዳድሮች ላይ የፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን የበላይነት እንዳለው ሊደነገግ ይገባል። በኢትዮጵያ ብቸኛው የሉዓላዊነት ባለቤት የፌዴራል መንግሥቱ ነው። ክፍላተ ሀገር (ኦሕዴድ/ብልፅግና ክልል የሚላቸው) ከመስተዳድርነት የዘለለ ሥልጣን ሊኖራቸው እንደማይገባ ባልደራስ ያምናል። ለዚህም እየታገለ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።

ባልደራስ የአዲስ አበባ ኗሪዎች የመኖሪያ ቤት እና የከተማ መሬት ባለቤት መሆን እንዳለባቸው ያምናል። መሬት የመንግሥት መሆኑ ቀርቶ የዜጎች መሆን አለበት። ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ሊሆን ይገባል። ለዚህም ፓርቲው እየታገለ ነው። የአዲስ አበባ ኗሪዎች ሁሉ እኩል ናቸው። በአዲስ አበባ ላይ ማንኛውም አካል ልዩ ጥቅም ሊኖረው አይገባም። ከተማችን ራስ ገዝ እንድትሆን ባልደራስ ይታገላል።

ፓርቲው ሀብትን ከማከፋፈል ይልቅ ሀብት መፍጠር ላይ ያተኮረ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ያምናል። ለዚህም የግሉን ክፍለ ምጣኔ ሃብት ማጠናከር ያስፈልጋል።

ኦ.ነ.ግ. እና ሕ.ወ.ሓ.ት. ሰራሹን ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ ሂደት መናድ፣ አባቶች ያወረሱንን ታሪክና ቅርስ ተንከባክቦ ማስቀጠል፣ ፍትሕና ዴሞክራሲን ማስፈን፣ እምነትን መጠበቅ፣ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአንክሮ የሚታገልባቸው አምዶች ናቸው።

 እሴቶች እና መርሆዎች


የግለሰብ ነፃነት !


ባልደራስ በኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግለሰብ ዲሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቱ ሙሉ በሙሉ የሚከበርበትን ስርዓት መፍጠር ዋነኛው ትኩረቱ ይሆናል፡፡ ከሁሉም በላይ የሆነዉ የሰዉ ልጅ እሴት ነጻነት እንደመሆኑ ህብረታችን ለግለሰብ ነጻነት ቀዳሚዉን ትኩረት ይሰጣል። ማንኛውም ሰው የግል ስብዕናውን እንዲያሳድግ እንዲሁም በግል ህይወቱ ግላዊ ሚስጥሩ በህግ እንዲጠበቅ ይደረጋል፡፡

በህይወት የመኖር መብት !

በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ በማንኛውም ቦታ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ዜጋ በህይወት የመኖር መብቱ እና የአካል ነፃነቱ የማይጣስ፣ ሰብዓዊ ሆኖ በመፈጠሩ ያገኘው የማይገሰስና የማይደፈር መብቱ በመሆኑ፣ ጥምረታችንን ለዚህ መበት መከበር ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡

እኩልነት !

ሰዎች ሲፈጠሩ እኩል ሁነው የተፈጠሩ እንደመሆናቸው ሁሉ ኢትዮጵያዉያን በዘውግ ልዮነት፣ በቆዳ ቀለም፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፆታ፣ በፖለቲካ፣ በሃብት ወይም በሌላ ምክንያት ልዩነት ሳይደረግባቸው በሕግ ፊት እኩል ከመሆናቸውም በላይ፣ እኩል የህግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡

የህግ የበላይነት !

ማንኛውም ሰው ከህግ አግባብ ውጭ አያያዝም፣ አይታሰርም፣ አይቀጣም እንዲሁም ሰውነቱም ሆነ የግል ንብረቱ ከህግ አግባብ ውጭ አይፈተሸም፡፡
በመንግስት ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ባለስልጣኖችም ሆኑ ማናቸውም ተራ ዜጋ በህግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ ማናቸውም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለህግ የበላይነት የመገዛት ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ማናኛውም ኢትዮጵያዊነት መልካም ስምና ክብርን ከሚያዋርድ ኢ- ሰብአዊ የጭካኔ አያያዝ ይጠበቃል ትጠበቃለች፡፡

ጠያቂነት እና ኃላፊነት!

ማናቸውም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰብ ለሚወስኑት ጉዳይ እና ለሚፈፀሙት ተግባር ተጠያቂነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ማናቸውም የሚሰጥ መብት በእላፊነት ጥቅም ላይ ሲውል በኃላፊነት ሊያስጠይቅ ይገባል፡፡
ይህ ኃላፊነት
– ግልሰቦች እርስ በእርሳቸው እና ከማህበረሰብ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት
– የሲቪክ ማህበራት እና ማናቸውም ስብሰቦች እርስ በእርሳቸውና ከህብረተሰቡ ጋር በበላቸው ግንኙነት
– መንግስት ራሱ ከሚያስተዳድረው ህዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ይሆናል፡፡

የዲሞክራሲያዊ መብቶች !

– ማንኛውም ሰው የህሊና እና የእምነት ነፃነቱ ይከበራል፡፡ አመለካከቱን በነፃነት የመግለፅ መብቱ ሊታፈን አይገባም፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የራሱን ሕይወት በሚነካ ውሳኔ ላይ ሃሳብ የመስጠት መብት ሊኖረው ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃሳቡን በንግግር እና በፅሑፍ የመግለፅ፣ ከሌሎች ጋር በመሆን የመሰባሰብ፣ የመወያየትና የመደራጀት፣ በሰላማዊ ሰልፍ እና መሰል ሕጋዊ እርምጃዎች የሚገለፅ ተቃውሞ የማድረግ መብቱ እንዲከበር እናደርጋለን፡፡ መንግስትን በመምረጥ እኩል ተሳትፎ ማድረግ፣ በሥራ ቦታ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ትርጉም ያለው ተሳትፎ የማደረግ መብት ሊኖረዉ ይገባል የሚል የፀና እምነት አለን፡፡

ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ ማስተናገድ !

ባልደራስ በሀገራችን ውስጥ የተለያዩ ቅርፅ እና መልክ ያላቸው ልዩነቶች እንዳሉ ይገነዘባል፡፡ እነዚህን ልዩነቶች አንድነታችንን ሳያናጉ ሊስተናገዱ የሚችሉበት አውድ እንዲፈጠር ባልደራስ በፅናት ይሰራል፡፡ ልዩነት በተፈጥሮም ሆነ በማህበራዊው ዓለም ውስጥ ያለና ሊታለፍ የማይችል ክስተት መሆኑን በመገንዘብ፣ ልዩነትን በኃይል ሳይሆን በውይይትና በሰለጠነ መንገድ የመፍታትና የማስተናገድ ልማድን ማዳበር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል፡፡

አርአያነት ያለው ስብዕና !

ሁላችን የኢትዮጵያ ዜጎች የወደፊት ህልውናች፣ እድገታችን እና የጋራ ደህንነታችን ከመከፋፈል ሳይሆን በአንድነት ከመቆም የሚመነጭ መሆኑን በመገንዘብ፣ ካከፋፋይ አመለካከት ራስን መጠበቅ፣ ለሌላው ዜጋ ችግር ተቆርቋሪ መሆን፣ በማናቸውም ግንኙነታችን ግልፅነትን፣ ሃቀኝነትን መላበስ እና ተጠያቂነትን የማክበር ባህል ልናዳብር ይገባል፡፡

ቅርስና ታሪክን መጠበቅ !

ባልደራስ ለኢትዮጵያ ቅርሶችና እሴቶች ትልቅ ክብር አለው፡፡ መንግስት ቅርሶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት፡፡ ባለፉት ጊዜያት በነበሩት የሃገራችን የፖለቲካ ለውጦች ያጣናቸው ወርቅዬ እሴቶች በሙሉ ለዘላለም ላይመለሱ ይጠፋሉ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ እሴቶቻችንን መመለስ የተቆረጡትን መቀጠል እንችላለን፡፡ ባልደራስ የተቆረጡ እሴቶችን ለመቀጠል የሚያስችል ፖሊሲ /Restoration of culture and heritages/ እቅድ አለው፡፡

ራዕይና ተልዕኮ !


ራዕይ !

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሃገራችን ኢትዮጵያ ወርድና ስፋት በእየሥልጣን እርከኑ የመንግሥት ስልጣን ምንጭ፣ ባለቤት፣ ተቆጣጣሪ እና ገሪ እንዲሆን እንሻለን የኢትየጵያ ዜጎች ስብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የተከበሩበት፣ ለመላ ሕዝቡ ፍላጎት መሟላት በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ የሚሰራ መንግስታዊ አመራር እንዲኖር እናልማለን፡፡ ሕዝቡ በማንነቱ ሳይለያይ በአንድ ሃገር ልጅነት እና በዜግነት የእኩልነት መንፈስ፣ የሃገሩ አንድነት እና ሉዓላዊነት ተጠብቆ ለትውልድ የሚተላልፍበትን ሁኔታ እውን ሁኖ ማየት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትና የልማት እንቅስቃሴ ስኬት ቀጣይነት ባለው ጠንካራ እና ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ በስፋት በተሳሰረ በውድድር ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት እውን ሆኖ ማየት ነው፡፡ የሃገሪቱ ኢኮኖሜ ሃብት አምራችና የሥራ ፈጣሪ የሆኑትን ብቻ በማበልፀግ የሚወሰን ሳይሆን፣ የሃገሪቱ ሃብት ማህበራዊ ፍትህን ባረጋገጠ መልኩ የመላ ሃገሪቱን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚውልበት፣ የሃገሪቱ ብልፅግና ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊ እና የባህላዊ ተሃድሶ የሚያካተትበት ሁኔታ እውን ሁኖ ማየት ነው፡፡

ተልዕኮ !

አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተቀይሮ ሕዝቡ በስፉት ተወያይቶ በሚያፀድቀው ሕገ መንግስት እንዲተካ ማድረግ፣ የሃገሪቱ የመንግስት አወቃቀር ከቋንቋ ወደ ጂኦግራፊያዊ አወቃቀር እንዲለወጥ እንታገላለን፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገባነት፣ ለፍትህ እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ፣ ለተሻለ ሕይወታቸው የሚተጋ፣ ለሕዝቡ ደህንነት እና ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ሳይታክት የሚሰራ መንግስት እንዲመሰረት ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪ የፓለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ነፃ ትክክለኛ እና ግልፅ በሆነ መንገድ የሚወዳደሩበት የምርጫ ስርዓት እንዲገነባ እንታገላለን፡፡

የትምህርት ስርዓቱ ሕዝብን የሚያራርቅ ሳይሆን የሚያቀራርብ እንዲሆን፣ ዜጎች ለሀገራቸው ታሪክ ፍቅር እንዲኖራቸው፣ የዜግነት ክብርና ኩራት እንዲሠማቸው፣ ሙያዊ ብቃትን እንዲላበሱ፣ በስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ የሚያስችል እንዲሆን እናደርጋለን፡፡

ለብሄራዊ እንድነት፣ ለሃገር ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ለዘላቂ ልማት የሚያመች ጤናማ ሃገራዊ ምህዳር እንዲኖር ብሔራዊ እርቅ እንዲደረግ ሁኔታዎችን እንዲመቻቹ እንጥራለን፡፡ በነፃነት የሚያስብና ለመብቱ የሚቆም ሕብረተሰብ መመሰረት፣ የሃገራችን ወጣት ትውልድ ከተስፋ መቁረጥ እና ከባከነ አኗኗር ተላቆ በራሱ እና በሃገሩ የሚኖረውን የኩራት መንፈስ እንዲያዳብር ባለማሳለስ እንሠራለን፡፡ ወጣቱ ትውልድ በሕይወቱ ጥሩ ተስፋ እንዲሰንቅ እና ለከፍተኛ ግብ ራሱን እንዲያነሳሳ መርዳትና እናደፋፍራለን፡፡