ባልደራስ Balderas logo
  • ዋና ገጽ
  • ዜና
  • ጋዜጣዊ መግለጫ
  • ፖ/ፕሮግራም
  • ምርጫ 2013
  • ባልደራስ ጋዜጣ
  • አባል ይሁኑ

About Us | Contact Us | Sitemap |
May 31, 2021

እነ እስክንድር ነጋና ጠበቆቻቸው በሌሉበት ምስክሮችን እንዲሰማለት ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠየቀ

ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 22 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል

በቃሊቲ ወህኒ ቤት በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) መሪዎች ማለትም እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ዛሬ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። በባልደራስ የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎችም ችሎቱን ታድመዋል። የኅሊና እስረኞችን በመወከል አቶ ስንታየሁ ቸኮል ችሎቱን ለታደሙ የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪዎች በችሎቱ ፊት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አቶ እስክንድር ነጋ ባለፈው ግንቦት 17 የዋለውን ችሎት በአርምሞ ተከታትለው የወጡ ሲሆን ዛሬም በእሳቸው መዝገብ ከተከሰሱ ሁሉም የኅሊና እስረኞች በተለየ በዝምታ ሲከታተሉ ውለዋል። በአንፃሩ ክርክሩን በንቃት ወረቀት ላይ ሲፅፉ አስተውለናል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ወደ እስር ፍርድ ቤት መልሶ በላከው መሰረት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በግልፅ ችሎት ቢቀርቡ ዐቃቤ ሕግ ሊደርስባቸው ይችላል ባላቸው ስጋቶች ላይ ክርክር ተደርጓል። ዐቃቤ ሕግ ‘የስጋት ትንተና’ ያለው፤ ነገር ግን በይዘቱ ጥቅል የሆነ ጉዳይ ከዚህ ችሎት አስቀድሞ ለዳኞች በፅህፈት ቤት በኩል በፅሁፍ ቀርቧል። በተመሳሳይ የኅሊና እስረኞች ጠበቆችም ስጋቱን ፉርሽ ያደረገ መከራከሪያ በፅሁፍ አቅርበዋል። ዛሬ የዋለው ችሎት የፅሁፍ ክርክሮችን ማብራራት ላይ ያተኮረ ሲሆን ከወትሮው ረዘም ያለ ጊዜም ወስዷል።

ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ 699/2003ን በመጥቀስ አምስት ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ማንነታቸው ሳይታወቅ እንዲመሰክሩለት እንዲሁም 16ቱ በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩለት ጠይቋል። ከዚህ በፊት በቅድመ ምርመራ ወቅት ምስክሮች በዝግ ችሎት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ አንድ ምስክር ላይ በሽጉጥ የግድያ ሙከራ መደረጉን ገልጿል።

ይህ የግድያ ሙከራ እንዴት፣ የት እና በማን እንደተፈፀመ ከተሰየሙት ሶስት ዳኞች መካከል የቀኝ ዳኛዋ ላነሱት ጥያቄ ዐቃቤ ሕግ ምላሽ አልሰጠም። በተመሳሳይ አስቴር ስዩም “የግድያ ሙከራው እንዴት ተደረገ? ማን ነው ያደረገው? የባልደራስ አመራር፣ አባል፣ ደጋፊ ነው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ዐቃቤ ሕግ ይህንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ባደረጋቸው ንግግሮች መልስ ሳይሰጥ አልፎታል። በመጨረሻም ሰብሳቢ ዳኛው ለዚህ ጥያቄ መልስ እንዲሰጡ በችሎቱ የተሰየሙ ሦስት ዐቃቤ ሕጎችን ቢጠይቁም ምላሽ አልተሰጣቸውም።

“ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ምስክሮች ከዚህ በፊት ዛቻ እና የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ከሆነ ይታወቃሉ ማለት ነው። የሚታወቁ ከሆነ ከመጋረጃ ጀርባ እና በዝግ ችሎት መቅረባቸው እንዴት ከጥቃት ሊያድናቸው ይችላል? በማለት ችሎቱ ጠይቋል። “ተከሳሾች ታዋቂዎችና ብዙ ደጋፊዎች ያሏቸው በመሆኑ ደጋፊዎቻቸው ጉዳት ያደርሱባቸዋል” ከማለት በዘለለ ዐቃቤ ሕግ አላብራራም። ከመጋረጃ ጀርባ እና የዝግ ችሎት አስፈላጊነትን በተመለከተም ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቆ “ምስክሮቻችን በግልፅ ችሎት የመመስከር ፍላጎት የላቸውም” ብሏል። በግልፅ ችሎት የሚመሰክርለት እማኝ አለማግኘቱንም ጠቁሟል።
በተያያዘ “ምስክሮች በግልፅ ችሎት ከቀረቡ ስማቸውን እና ምስላቸውን በፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማራጮች በማሰራጨች ማህበራዊ መገለል ያደርሱባቸዋል” ሲል ስጋቱን ጠቁሟል። ጠበቆች በበኩላቸው “አንድ ሰው ከሚኖርበት ማህበረሰብ እሴት ሲያፈነግጥ ማህበረሰቡ ራሱ ማህበራዊ ቅጣት ይቀጣል። ይህ በማህበረሰብ እሴት እንጂ በሕግ የሚታይ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ እነ እስክንድር ነጋ እና ጠበቆቻቸው በሌሉበት ችሎቱ በምስጢር የምስክሮቹን ቃል እንዲቀበልለትም ጠይቋል። ይህንን የሰሙት ወይዘሮ አስቴር ስዩም “እንዲህማ ከሆነ ዐቃቤ ሕግ ራሱ አይፈርድም ወይ፤ ፍርድ ቤቱ ግራና ቀኙን ማየት የለበትም ወይ?” በማለት ቢጠይቁም በቀጣዩ ችሎት ምላሽ እንደሚሰጣቸው ገልፀው ዳኞች አልፈውታል።

የምስክሮች ስጋት ያላቸውን ዐቃቤ ሕግ በዝርዝር አለማቅረቡን ያስረዱት ጠበቆች በንፅፅር የዩጎዝላቪያን ተሞክሮ አብራርተዋል። በዩጎዝላቪያ ተፈፀመ በተባለ ወንጀል ምስክሮች በስውር እንዲቀርቡ ተጠይቆ ስጋቶች በተጨበጫ መቅረብ ስላልቻሉ ጥያቄው ውድቅ መደረጉን አስረድተዋል። በእነ እስክንድር ነጋ ዶሴ ላይ ዐቃቤ ሕግ እያቀረበው ያለው ጥያቄ ከዓለም ዓቀፍ የፍርድ ስርዓት ውጭ መሆኑንን ተናግረዋል።

ይህንን ያከራከረው ፍርድ ቤቱ ከመጭው ምርጫ በኋላ ለሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። የምርጫ እንቅስቃሴው ካለፈ በኋላ በርካታ ታዳሚዎች ባሉበት ለመፍረድ እንደሚያመቻቸውም ሰብሳቢ ዳኛው ተናግረዋል። ከአንድ ወር በኋላ ቀጣዩ ችሎት በተደረገ ከ2 ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የፍርድ ቤቶች ዓመታዊ ረፍት የሚደረግበትና ዝግ የሚሆኑበት ጊዜ እንደሚጀምር ይታወቃል።

6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እንዲታገድ ባልደራስ ፍርድ ቤትን ጠየቀ ! ዶ/ር ብርሃኑ ዘለቀ

Related Posts

ዜና, የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ

የባልደራስ ድጋፍ ሰጪ በሰሜን አሜሪካ

ህመሙ _አመመኝ

ዜና, የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ

ህመሙ _አመመኝ

የእስክንድር እግር መሰበሩ በህክምና ተረጋገጠ !

ዜና, የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ

የእስክንድር እግር መሰበሩ በህክምና ተረጋገጠ !

Recent Posts

  • የባልደራስ ድጋፍ ሰጪ በሰሜን አሜሪካ October 23, 2021
ባልደራስ Balderas logo
  • ዋና ገጽ
  • ዜና
  • ጋዜጣዊ መግለጫ
  • ፖ/ፕሮግራም
  • ምርጫ 2013
  • ባልደራስ ጋዜጣ
  • አባል ይሁኑ

ድል ለዲሞክራሲ!!!

© ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ Balderas for true democracy 2021